30/01/2026
ፎልክ ኑቮ (Folk Nouveau)፦ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተላበሰ ዓለም አቀፋዊ የዲዛይን አቅጣጫ
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ የዲዛይን ኢንዱስትሪ ውስጥ ረቂቅ ግን ደግሞ ጥልቅ የሆነ ለውጥ እየታየ ነው። ላለፉት ዓመታት ገነን የነበረው ቅዝቃዜ የሚሰማው "ሚኒማሊዝም" (Minimalism) አሁን ቦታውን ለሞቃታማ፣ ባለታሪክ እና ገላጭ ለሆኑ ዲዛይኖች እየለቀቀ ነው። ይህ አዲስ እንቅስቃሴ ስም ተሰጥቶታል፦ ፎልክ ኑቮ (Folk Nouveau)።
ይህንን ዘይቤ በመጽሔቶች፣ በኤግዚቢሽኖች እና በታዋቂ የቤት ውስጥ ዲዛይኖች ላይ ደጋግሜ ስመለከተው በውስጤ ፈገግ አልኩ። ምክንያቱም ይህ "አዲስ" የተባለው ትሬንድ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን በጣም ቅርባችን እና የታወቀ ስሜት ስላለው ነው። ለዚህም ነው ይህንን ሀሳብ ለወገኖቼ ላካፍል የወደድኩት።
ፎልክ ኑቮ የ"አርት ኑቮን" (Art Nouveau) ለስላሳ ኩርባዎች ከባህላዊ እደ-ጥበባት እና ከታሪካዊ ትረካዎች ጋር ያዋህዳል። በሰው እጅ የተሰሩ፣ የጊዜ አሻራ ያለባቸውን እና ትርጉም ያዘሉ ቁሶችን ያከብራል። ፍጹም የተስተካከለ ሳይሆን፣ "ነፍስ" ያለው ጥበብ ላይ ያተኩራል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከዲዛይን ጋር አብሮ የመኖር ባህላችን ገና ድሮም እንዲህ ነበር።
በጥንቃቄ የተጎነጎኑ ሰፈዶች አሁን እንደ ግድግዳ ጌጥ ወይም እንደ መብራት ማጌጫ ተቀይረው ሲቀርቡ ይታያሉ።
የቡና ስነ-ስርዓት ማድመቂያ የነበሩት ጀበናዎች እና የሸክላ ውጤቶች አሁን እንደ የአበባ ማስቀመጫ ወይም እንደ ዘመናዊ የማስጌጫ ቁሶች ሆነው ብቅ ብለዋል።
ከቆዳ የተሰሩ ምንጣፎች እና በኢትዮጵያዊ ቅርጾች የተቀረጹ የእንጨት ወንበሮች የቤቱ ዋነኛ የጥበብ ውጤቶች ናቸው።
ምግብ በጋራ የምንበላበት መሶብ እንኳን ሳይቀር አሁን እንደ ጎንዮሽ ጠረጴዛ (Side table) ወይም ለቤት ድምቀት የሚሰጡ "Statement pieces" ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ።
ይህ በንጹህ መልክ የሚገለጽ ፎልክ ኑቮ ነው። አሮጌ ታሪኮች በአዲስ ቋንቋ ሲተረኩ ማለት ነው። ይህንን መሰል ታሪክ ቀደም ሲል በባህላዊ ውዝዋዜዎቻችን ላይም አይተነዋል። ለትውልዶች ስንጨፍራቸው የኖርናቸው ውዝዋዜዎች ዛሬ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እንደ አዲስ "ፈጠራ" ተደርገው ሲቀርቡ እናያለን። ዲዛይንም ከዚህ የተለየ አይደለም።
ፎልክ ኑቮ የቆየ ማንነታችን ቢሆንም፣ እነዚህን የባህል ቁሶች ከዘመናዊ ፈርኒቸር ጋር አቀናጅቶ፣ ቤትን እንደ ሙዚየም ሳይሆን እንደ ዘመናዊ መኖሪያ የማስዋብ ጥበብ ግን የዲዛይነር አይንን ይጠይቃል።
በቤታችሁ ውስጥ የትኛውን ቀለም ከየትኛው ጨርቅ፣ የትኛውን ሰፈድ ከየትኛው ግድግዳ ጋር ማዋሃድ እንዳለባችሁ የምመክራችሁባቸው የዲዛይን 'Secret Tips' አሉኝ። እነዚህን ሚስጥራዊ መመሪያዎች እንድልክላችሁና ቤታችሁን አብረን እንድንቀይር... ኮሜንት ላይ የ"ፎልክ ኑቮ" ዘይቤን በኢትዮጵያዊ ቤት ውስጥ እንዴት መተግበር ይቻላል? ብላችሁ ጠይቁኝ።