17/04/2026
✝️✝️ዓርብ ~ ቤተክርስቲያን
✍️ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል በዘይቤያዊ ፍቺ ሦስት ዓይነት ትርጉም አለው።
ይህም፦
፩ኛ, የክርስቲያን ቤት የክርስቲያን መሰብሰቢያ ማለት ነው። ይህም ማለት ክርስቲያኖች በአንድነት በመሰብሰብ ሥርዓተ አምልኮትን የሚፈጽሙበት ቦታ መሆኑን ያመለክታል። (ኢሳ ፶፮፥፯ ፣ ኤር ፯፥፲-፲፩ ፣ ማቴ ፳፩፥፳፫ ፣ ማር ፲፩፥፲፯ ፣ ሉቃ ፲፱፥፵፱)
፪ኛ, የክርስቲያኖች ስብስብ የክርስቲያኖች አንድነት ማለት ሲሆን "ቤተ እስራኤል ፣ ቤተ ያዕቆብ ፣ ቤተ አሮን" ሲል የእስራኤል ወገን፣ የያዕቆብ ወገን፣ የአሮን ወገን ማለት እንደሆነ ሁሉ ቤተክርስቲያን ሲባልም የክርስቲያን ወገን ማለት ነው። (መዝ ፻፲፯፥፫ ፣ ማቴ ፲፮፥፲፰ ፣ ማቴ ፲፰፥ ፲፯ ፣ ራእ፩፥፲፩)
፫ኛ, እያንዳንዱ ክርስቲያን ቤተክርስቲያን ይባላል። ይህም ቤተመቅደስ (ቤተክርስቶስ) ለማለት ነው።(፩ኛ ቆሮ ፫፥፲፮፣፲፮፥፲፮ ፣ ፪ኛ ቆሮ ፮፥፲፮)
በአጠቃላይ አነጋገር የቤተክርስቲያን ሥርዓት ሲባል የክርስቲያኖች ሕግ ፣ ቀኖና አሠራር ማለት ነው።
✔️ታዲያ ጌታችን በተነሣ በስድስተኛው ቀን ቤተክርስቲያን ተብሎ መከበሩ ጌታችን በመስቀል ተሰቅሎ ደሙን አፍሶ ቤተክርስቲያንን የመሠረተ መሆኑን ለማሰብ ነው።
✍️ለዚህም መነሻው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። "ወይእዜኒ ዕቀቡ ርእሰክሙ ወኵሎ መራዕየ ዘሎቱ ሤመክሙ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳተ ከመ ትርዐዩ ቤተ ክርስቲያኑ ለእግዚአብሔር እንተ አጥረያ በደሙ "
🔐ትርጉም
"አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ"(ሐዋ፳፥፳፰) የሚለውና ሌላውም ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ አማናዊ ቃል ነው።
✍️ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማዕከለ ምድር በቀራንዮ ሲሰቀል ከተወጋው ጎኑ የፈሰሰውን ክቡር ደም መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል በብርሃን ጽዋዕ ቀድቶ በዓለም ነዝቶት/ረጭቶት ነበርና ደሙ በነጠበበት ሁሉ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ቤተክርስቲያን ስትሠራ ትኖራለች። ድርሳነ ዑራኤል ገጽ ፻፶፰ ቁጥር ፳፪ ይመልከቱ።